የኢህአዴግ ምክር ቤት የፓርቲውን ውህደት አፀደቀ ― የኢትዮጵያ ብልጽግና ፓርቲ እውን ይሆናል

Home Forums Semonegna Stories የኢህአዴግ ምክር ቤት የፓርቲውን ውህደት አፀደቀ ― የኢትዮጵያ ብልጽግና ፓርቲ እውን ይሆናል

Viewing 1 post (of 1 total)
  • Author
    Posts
  • #12737
    Semonegna
    Keymaster

    አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ) ምክር ቤት የግንባሩ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ የመራለትን የፓርቲውን ውህደት አፀደቀ። የምክር ቤቱ ስብሰባ በህዳር 11 ቀን 2012 ዓ.ም. ውሎው ኢህአዴግና አጋር ድርጅቶችን በማዋሃድ አንድ አገር አቀፍ ፓርቲ (የኢትዮጵያ ብልጽግና ፓርቲ) ለመመሥረት በተጀመረው እንቅስቃሴ ላይ ትኩረት አድርጎ ከተወያየ በኋላ ነው ያጸደቀው።

    ኢህአዴግ በሥራ አስፈጻሚ ደረጃ ግንባሩ ከአጋሮቹ ጋር እንዲዋሃድና ህብረ-ብሔራዊ ፓርቲ እንዲሆን ሰሞኑን በአብላጫ ድምጽ በመወሰን ለምክር ቤቱ መምራቱ ይታወሳል። ውህዱ ፓርቲ “የኢትዮጵያ ብልጽግና ፓርቲ” የሚለውን ስያሜ ተሰጥቶት ለኢህአዴግ ምክር ቤት እንዲቀርብ የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴው ከስምምነት መድረሱም ይታወሳል። ምክር ቤቱም ህዳር 11 ቀን ባካሄደው ስብሰባው ግንባሩና አጋር ድርጅቶቹ እንዲዋሃዱ ውሳኔውን አሳልፏል።

    የኢሕአዴግ ምክር ቤት ዛሬ የፖርቲውን ውሕደት አጽድቋል። በአዲሱ የብልጽግና ፓርቲ አማካኝነት ሁሉም የታላቋ ኢትዮጵያ ዜጎች የሚሳተፉበት ጠንካራ፣ አካታችና እውነተኛ የፌደራል ሥርዓት ለመፍጠር ቆርጠን ተነሥተናል። ጸንተንም እንታገላለን።ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በትዊተር/ፌስቡክ ገጻቸው ላይ

    የኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ አባል አቶ ፍቃዱ ተሰማ የህዳር 11 ቀን የምክር ቤቱን ውሎ በማስመልከት ለኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (ኢቢሲ) እንደተናገሩት፥ ምክር ቤቱ በፓርቲው ውህደት ዙሪያ ተወያይቶ በሙሉ ድምጽ አጽድቋል። አቶ ፍቃዱ እንደገለጹት ምልዓተ ጉባዔው ተሟልቶ ከመከረ በኋላ ውህደቱን በሙሉ ድምጽ ነው ያጸደቀው።

    በውይይቱ ላይ የኢህአዴግ ኦዲትና ቁጥጥር ኮሚሽንም የውህደቱን አስፈላጊነት፣ ሕጋዊ አሠራርና ከደንቡ ጋር የተገናኙ ጉዳዮችን በተመለከተ ዝርዝር ጥናት ማቅረቡን ነው የገለጹት።

    በኮሚሽኑ ጥናት ውጤት መሠረትም ኢህአዴግ አገራዊ ለውጡን ለመምራትና መሠረት ለማስያዝ፣ እንዲሁም ሁለንተናዊ ብልጽግና ለማረጋገጥ የውህደቱ አስፈላጊነት ላይ ከስምምነት ተደርሷል። የውህደቱ ሂደትም ሕገ-ደንቡና ስርዓቱን የተከተለ መሆኑ ተረጋግጦ ምክክር ከተደረገበት በኋላ መጽደቁን አብራርተዋል።

    ምክር ቤቱ በሁለተኛ ደረጃ የተመለከተው የኢትዮጵያ ብልጽግና ፓርቲ መርሀ-ግብርን (ፕሮግራምን) ሲሆን፤ ፓርቲው በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚ፣ በማኅበራዊና በውጭ ግንኙነት ላይ የሚከተላቸውን አቅጣጫዎች በሰፊው መመልከቱን አብራርተዋል።

    ቀደም ብሎ የኢህአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ፓርቲው በመተዳደርያ ደንቡ ላይ በአገሪቷ ለሚገኙ ቋንቋዎች በሙሉ እውቅና መስጠቱ ይታወሳል። ውህዱ ፓርቲም አማርኛን ጨምሮ አፋን ኦሮሞ፣ ሶማልኛ፣ ትግርኛ እና አፋርኛ ቋንቋዎች ለሥራ ቋንቋነት የተመረጡ መሆኑንም ማስታወቁ ይታወሳል።

    የኢትዮጵያ ብልጽግና ፓርቲ በፕሬዝዳንትና ምክትል ፕሬዝዳንት የሚመራ ሲሆን፤ ይህም ከዚህ ቀደም የነበረውን ሊቀ-መንበርና ምክትል ሊቀ-መንበር የሚሉትን ስያሜዎችን ይተካል።

    ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ)/ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ 

    የኢትዮጵያ ብልጽግና ፓርቲ

Viewing 1 post (of 1 total)
  • You must be logged in to reply to this topic.