ከትግራይ ብልፅግና ፓርቲ በወቅታዊ ጉዳይ ላይ የተሰጠ መግለጫ

Home Forums Semonegna Stories ምርጫ በኢትዮጵያ ― የኢትዮጵያ ብሔራዊ እና ክልላዊ ምርጫዎች ― ሰሞነኛ ዜናዎችና መረጃዎች ከትግራይ ብልፅግና ፓርቲ በወቅታዊ ጉዳይ ላይ የተሰጠ መግለጫ

#14559
Anonymous
Inactive

በወቅታዊ ጉዳይ ላይ የትግራይ ብልፅግና ፓርቲ የሰጠው መግለጫ

ከሁሉ አስቀድመን በመቐለ ከተማ በጠራራ ፀሀይ ክልሉን እየገዛ ባለው ፓርቲ በታጠቁ ሀይሎች በጥይት ተደብድቦ በተገደለው ትግራዋይ ወጣት የተሰማንን ጥልቅ ሀዘን እየገለፅን፤ ለቤተሰቦቹ ለወዳጆቹና ለአብሮ አደግ ጓደኞቹ እንዲሁም ለሰላም ወዳድ የትግራይ ሕዝብ መፅናናትን እንመኛለን።

በአሁኑ ሰዓት አገራችን ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተከሰተዉ ገዳይና አሰከፊ የሆነዉን የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ከሕዝብ ጋር በመሆን የመከላከል እና ሕዝብን የማዳን ሥራ እተሠራ ይገኛል።

በዚሁ ሁኔታ መንግሥትና ፓርቲያችን ዘርፈ-ብዙ የሆኑ የሪፎርም ሥራዎችን በማከናወንና በመተግበር ላይ ይገኛል። ከእነዚህ ጉልህ ዘርፈ ብዙ አወንታዊ ዉጤቶች ባሻገር የተለያዩ ችግሮችና ተግዳሮቶች አብይ ፈተና ሆነዋል። በተለይም በግጭት አትራፊዎች በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በሚፈጥሩትና በሚቀሰቅሱት ግጭቶችና ሁከቶች ክቡር የሆነውን የሰው ልጅ ሕይወት ሲቀጥፍ መመልከት እየተለመደ መጥቷል። ይህም ድርጊት ለሕዝቦች ሆነ ለሀገራዊ አንድነት የማይበጅ እንዲሁም አሳዛኝ ድርጊት ነዉ።

ሕዝባችን በዚህ ፈታኝ ወቅት ያጋጠመውን ድርብ ፈተናና ችግር በማለፍ ወደሚፈልገውና ወደሚገባው የሰላም፣ የብልጽግና የመረጋጋት፣ የዲሞክራሲና የልማት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በመንግሥት ሆነ በፓርቲ በተለያዩ ደረጃዎች የሚገኙ የመንግሥት አመራሮችና ሠራተኞች ሕዝባዊነታቸው፣ የአመራር እሴቶቻቸውና ጥበባቸው የሚፈተንበት ታሪካዊ ጊዜ ላይ እንደምንገኝም ማስተዋልና መበርታት ይገባል።

ሆኖም መንግሥት ከሕዝብ ጋር በመሆን ችግሮችንና ተግዳሮቶችን በመለየትና ቅድሚያ በመስጠት እንዲሁም የስጋት ደረጃና መጠኖችን በመመርመርና በመፈተሽ ዘላቂ መፍትሔ ለማምጣት ያላሰለሰ ጥረት እየተደረገ ባለበት ሁኔታ ፀረ ለውጥና ጸረ-ኢትዮጵያዊያን ኃይሎች ሆን ብለዉና አቅደዉ በተሳሳተ መንገድ ሕዝቡን በማደናገርና ወደ ጥፋት ጎዳና ለመምራት እየሠሩ ይገኛሉ።

በተጨማሪም ይህንን አስቸጋሪ የታሪክ አጋጣሚ ለግላዊ ጥቅማቸዉና ፍላጎታቸው ለማሟላት ሕዝብንም ሆነ ሀገርን የሚጎዱ አስነዋሪና አጸያፊ ተግባሮችን በመፈፀም ላይ እንደሚገኙ የአደባባይ ምስጢር ከሆነ ሰነባብቷል።

የትግራይ ሕዝብ የቅርብ ሆነ የሩቅ ታሪኩ እንደሚያሳየው፣ ጭቆናንም ሆነ አፈናን የሚፀየፍ ለኢትዮጵያ አንድነት መስዋዕት የከፈለ ሕዝብ ነው። በትግሉና በመስዋዕትነቱም ለመላው የሀገራችን ሕዝቦች ጉልህ ሕዝባዊ ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ የበኩሉን ድርሻ የተወጣና በመወጣትም ላይ ያለ ሕዝብ ነዉ። የትግራይ ሕዝብ ከሌሎች ሕዝቦች ጋር በአንድነት በመሆን ባካሄደው እልህ አስጨራሽ ተጋድሎ በከፈለው መስዋዕትነት የሰላምና ዲሞክራሲ ብልጭታ የማየት ፍላጎቱ በቀረበው ቁጥር የሚሸሽበት ምናባዊ ዓለም ብቻ እየሆነበት መጥቷል። ከሁለት ቀናት በፊት በመቐለ ከተማ የተከሰተው ለአንድ ወጣት ክቡር ሕይወት ህልፈትና ለሁለት ወጣቶች የመቁሰል አደጋ በክልሉ ዉስጥ የሰላምና ዲሞክራሲ እጦት ማሳያ ነዉ።

በሰላም ወዳዱና እንግዳ አክባሪ በሆነዉ የመቐለ ከተማ ነዋሪ መሪር የሀዘንና ውጥረት ድባብ ዉስጥ ይገኛል። ይህ ክቡር የሰው ሕይወት የጠፋበትና ከባድ የመቁሰል አደጋ ያጋጠመበት ክስተትም ሰላምንና ፀጥታን በሕግ አግባብ ለማስጠበቅ ኃላፊነት በተሰጠው የፀጥታ አካል የተፈፀመ መሆኑ እጅጉን በጣም አሳዛኝ ያደርገዋል። ይህም ድርጊት ብዙ መስዋዕት ለከፈለ የማይገባዉ ነዉ። በመሆኑም የወጣቱ ግብረመልስም በክልሉ ሰላምና ዲሞክራሲ ጉዳይ ላይ የኔ ጉዳይ ነዉ የሚል ከፍተኛ የሰላም፣ የልማትና የለውጥ ፍላጐቶችና ቁርጠኝነት እንዲሁም ዝግጁነት መኖሩን በግልፅ አሳይቷል።

እንደሚታወቀዉ በአስቸኴይ ጊዜ አዋጅ የማስተዳደርና የማሰፈፀም አግባቦች ውስጥ የሰው ልጅን ዲሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብቶችን ማክበርና በሕግ የማስከበር ተግባር ላይም የፀጥታ አካላት የላቀ ሰብአዊነት፣ ታጋሽነትና፣ ፍፁም ሕዝባዊነትን የተላበሱ መሆን ይገባቸዋል። የዲሞክራሲና የተሻለ የሰብዓዊ መብት አያያዝ ልምድ ጉዳይ ከአስተምህሮት ስርፀትና ግልፅ ተጠያቂነትን ከማስፈን አሠራር ጋር በቀጥታ የሚገናኝ ጉዳይ ሲሆን፤ ዜጎች በመንግሥታቸው የደኅንነት ስሜት እንዲሰማቸው የሚያደርግ ቢሆንም እንደ አለመታደል ሆኖ በትግራይ ክልል በወቅቱ የሚስተዋሉ ሕገ-ወጥ ክስተቶች አፈናና ግልፅ የሰብዓዊ መብት ረገጣ እንዳለ ማስተዋል ተችሏል። በተለይም እራሳቸውን ለመከላከል በማይችሉ ወጣቶች ላይ መተኪያ የሌለውን ክቡር ሕይወታቸዉን እስከመቅጠፍ የደረሰ የኃይል እርምጃ በየትኛውም መለኪያ መወገዝ ያለበትና ፈፅሞ ተቀባይነት የሌለው እኩይ ተግባር ነው። ድርጊቱም በፍጥነት ተጣርቶ የተወሰደው እርምት እርምጃ ለሕዝብ ይፋ እንዲደረግ አጥብቀን እንጠይቃለን።

ይህ እኩይ ተግባር በተለይ በክልሉ ወጣቶች ላይ ያነጣጠረ በመሆኑ፣ ይህን መሰል የአፈና ተግባር የክልሉ ወጣት ሰላማዊና ሕጋዊ በሆነ መልኩ አጥብቆ እንዲታገለው የትግራይ ብልጽግና ፓርቲ ጥሪውን እያቀረበ፤ በአጠቃላይ ሀገራዊ የለውጥ እንቅስቃሴዎች ላይ የነቃ ፖለቲካዊ ተሳትፎ በማድረግ በክልሉና በሀገር ደረጃ የተደቀኑ ችግሮችን ለመቅረፍ በምታደርጉት እንቅስቃሴ ፓርቲያችን ድጋፉ እንደማይለያችሁ ለመግለፅ እንወዳለን።

“ወደ ሕዝብ የተኮሰ ውድቀቱን አፋጠነ” እንደሚባለው፣ የገዢዎች የውድቀት ምልክት የሚጀምረዉ ወደ ሕዝብ መተኮስ የጀመሩ ዕለት ነው። ስለሆንም በትግራይ ክልል በተለይ ደግሞ በመቐለ ከተማ ባጋጠመው ክስተት፣ በክልሉ የዲሞክራሲና የሰብዓዊ መብት አያያዝ ጉዳይ የክልሉ ገዢ ፓርቲና መንግሥት አካሄዱን ቆም ብሎ እንዲመረምር አስገዳጅ ማንቂያ ደወል ነው። የትግራይ ብልፅግና ፓርቲም ጉዳዩን በአፅንኦት እንደሚከታተለውና ለሚመለከታችሁ ሁሉ በጥብቅ ያሳስባል።

በዚህ አጋጣሚ ለሁሉም የትግራይ ወጣት እና ለውጥ ፈላጊ ኃይል ከትግራይ ብልፅግና ፓርቲ ጋር በመሆን የለውጥ ሂደቱን እንዲያፋጥኑ ከፓርቲያችን ጋር እንድትቆሙ ጥሪያችንን እናቀርባለን። ፓርቲያችን የትግራይ ሕዝብ እንደማንኛዉም ኢትዮጵያዊ የሚገባዉን ጥቅም እንዲረጋገጥ እና ሃገራዊ አንድነቱ እንዲጠናከር ይሠራል። በጥቂት ገዥ የህወሓት ቡድን በተለይ በዝምድና እና ጥቅም ትስስር እንዲሁም በሥልጣን ጥማት ምክንያት ትግራይን ከሌሎች የሀገሪቱ ሕዝቦች ለመነጠል የሚደረግ ሥራም ሆነ ሴራ በጥብቅ የምንታገለዉና የምናወግዘዉ መሆኑን በጥብቅ እናሳዉቃለን።

በመጨረሻም ለሟች የዘለዓለም እረፍት፣ ለቤተሰብና ወዳጅ ዘመዶች መጽናናትን ከልብ እንመኛለን።

የትግራይ ብልፅግና ፓርቲ
ግንቦት 11ቀን 2012 ዓ.ም.

የትግራይ ብልፅግና ፓርቲ