የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ መከሰትን ተከትሎ 111 የንጽህና መጠበቂያ አምራቾች ዘርፉን ተቀላቅለዋል

Home Forums Semonegna Stories ኢትዮጵያ ውስጥ የኮቪድ-19 (ኮሮና ቫይረስ) ስርጭትን እና ለመከለከል የሚደረገውን ጥረት ወቅታዊ መረጃ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ መከሰትን ተከትሎ 111 የንጽህና መጠበቂያ አምራቾች ዘርፉን ተቀላቅለዋል

#14341
Anonymous
Inactive

የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ መከሰትን ተከትሎ 111 የንጽህና መጠበቂያ አምራቾች ዘርፉን ተቀላቅለዋል

አዲስ አበባ (ኢዜአ) – የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በሀገሪቱ ከተከሰተ በኋላ ለ111 የንጽህና መጠበቂያ አምራቾች ፍቃድ መስጠቱን የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን (የቀድሞው የኢትዮጵያ የምግብ መድኃኒትና ጤና ክብካቤ አስተዳደር ባለስልጣን (EFDA)) አስታወቀ።

የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ሄራን ገርባ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) እንደገለጹት፥ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በኢትዮጵያ ከተከሰተ በኋላ በሕብረተሰቡ ዘንድ የንጽህና መጠበቂያ ቁሶች ፍላጎት ጨምሯል። በወቅቱ የፍላጎቱና የምርት መጠን ባለመመጣጠኑ በተለይም የሳኒታይዘር እና የአልኮል ምርት እጥረት አጋጥሞ ነበር።

ችግሩን ለመፍታት ባለስልጣን መሥሪያ ቤቱ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመቀናጀት በዘርፉ ከተሰማሩና ፍላጎት ካላቸው አምራቾች ጋር ውይይት ማካሄዱንም አስታውሰዋል። በዚህም አምራቾች ሳኒታይዘር እና አልኮል በስፋትና በጥራት እንዲያመርቱ የሚያስችል ስምምነት ተደርጎ ወደ ሥራ የገቡበት ሁኔታ መኖሩን ነው ዋና ዳይሬክተሯ የተናገሩት።

ባለስልጣኑም አምራቾቹ ደረጃውንና ጥራቱን የጠበቀ ሳኒታይዘር እና አልኮል በስፋት እንዲያመርቱ ለማስቻል የሚያግዝ ጊዜያዊ መመሪያ አውጥቶ ተግባራዊ አድርጓል።

ዳይሬክተሯ እንዳሉት፥ መመሪያው አምራቹ ስለምርቱ ሁኔታና ጠቀሜታ የሚያቀርበው የቅድመ ተግባር ሀሳብ (proposal) በአጭር ጊዜ ተቀባይነት እንዲኖረው የሚያስችልና የፍቃድ አሰጣጥ ሂደቱም ፈጣን እንዲሆን የሚያግዝ አሠራርን በውስጡ አካቶ የያዘ ነው። በዚህ መሠረት ዘርፉን በመቀላቀል የጥራትና የግብአት መስፈርቱን ላሟሉ 111 አምራች ፋብሪካዎች ወደምርት እንዲገቡ ፈቃድ መሰጠቱን ወ/ሮ ሄራን አስታውቀዋል።

“ፋብሪካዎቹ በአሁኑ ወቅት የሳኒታይዘር እና የአልኮል ምርቶቻቸውን በጥራትና በሚፈለገው መጠን በማምረት ለሕብረተሰቡ እያቀረቡ ይገኛሉም” ብለዋል ወ/ሮ ሄራን።

የምርቶቹን የጥራትና የደረጃ ሁኔታ ለመከታተልም በጊዜያዊነት የተዘጋጀው መመሪያ የቅኝት ሥራን የሚያከናውኑ አካላት ቅንጅታዊ አሠራርን ዝርዝር ሁኔታ ጭምር የሚዳስስ ነው። የቅኝት ሥራውን ከባለስልጣን መሥሪያ ቤቱ ሙያተኞች በተጨማሪ ከአዲስ አበባ የምግብ መድኃኒትና ጤና ክብካቤ ባለስልጣን እና ከጸጥታ አካላት የተወጣጣ ግብረ ኃይል ተቋቁሞ የሚሠሩበት ሁኔታም ተፈጥሯል።

ወ/ሮ ሄራን እንደገለጹት፥ የቅኝት ሥራው በገበያ ስፍራዎች፣ በሸቀጣሸቀጥ መሸጫ ሱቆች፣ በሱፐር ማርኬቶችና በመድኃኒት ቤቶች የሚከናወን ነው። በተከናወነው የቅኝት ሥራም አጠራጣሪና ከደረጃ በታች የሆኑ፣ እውቅናና የንግድ ፈቃድ የሌላቸው እንዲሁም የጥራት ደረጃቸው ዝቅተኛ የሆኑ ምርቶችን በፍተሻ መያዝ ተችሏል።

“በዚህም ባለስልጣኑ እነዚህን ምርቶች ከገበያ የመሰብሰብና የማስወገድ ሥራ እና አቅራቢዎቹንም ተጠያቂ የማድረግ ተግባር አከናውኗል” ይላሉ ወ/ሮ ሄራን። በቁጥጥር ሥራው እርምጃ ከተወሰደ በኋላ የተወሰኑ አምራቾች የምርት ጥራታቸውን በማሻሻል በአዲስ መልክ ወደ ምርት ለመግባት እየተንቀሳቀሱ መሆናቸውንም አመልክተዋል።

ምንጭ፦ ኢዜአ/ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ