የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ከትግራይ ክልል ቀውስ ጋር በተገናኘ ተጨማሪ ማዕቀብ በኢትዮጵያ ላይ እንዲጣል አዘዙ

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ከትግራይ ክልል ቀውስ ጋር በተገናኘ ተጠያቂ ባደረጓቸው የኢትዮጵያ ፌዴራል መንግስትና የአማራ ክልል ባለስልጣናት ላይ እንዲሁም በህወሓት እና በኤርትራ መንግስት አመራሮች ላይ ተጨማሪ ማዕቀብ እንዲጣል አዘዙ።

ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ዛሬ በፈረሙት የስራ አስፈጻሚ አካል ትዕዛዝ የትግራይ ክልል ግጭት እንዲራዘም ፤ ለትግራይ ክልል ሰብዓዊ እርዳታ እንዳይቀርብ ያስተጓጎሉ እና የቶክስ አቁም ስምምነት እንዳይደረስ እንቅፋት ሆነዋል ባሏቸው ላይ ተጨማሪ ማዕቀብ እንዲጣል ወስነዋል።

ማዕቀቡ እንዲጣል ያዘዙትም ከላይ ለተጠቀሱት ጉዳዮች ተጠያቂ ናቸው በተባሉ የኢትዮጵያ ፌዴራል መንግስት እና የአማራ ክልል መስተዳደር ባለስልጣናት ላይ እንዲሁም በህወሓት እና በኤርትራ መንግስት አመራሮች ላይ እንደሆነ የአሜሪካ መንግስት ያወጣው መግለጫ ያመለክታል።

ተጠያቂ ናቸው የተባሉት የመንግስት ባለስልጣናት እና የህወሓት አመራሮች ማንነት ግን ይፋ አልተደረገም።

ይሁን እንጂ የአሜሪካ የመንግስት ግምጃቤት ከአገሪቱ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ጋር በመተባበር ተጠያቂ መሆን የሚገባቸውን እየለየ ማዕቀቡን ተግባራዊ የማድረግ ኃላፊነት ተሰጥቶታል።

ማዕቀቡ በተመረጡ ግለሰቦች ላይ ብቻ ተግባራዊ እንደሚደረግ እና የኢትዮጵያ ህዝብን በማይጎዳ መልኩ እንደሚተገበር የአገሪቱ መንግስት ያወጣው መግለጫ ያመለክታል።

ከዚህ ቀደም ተመሳሳይ የጉዞ ማዕቀብ በኢትዮጵያ የፌዴራል መንግስት አመራሮች እና የህወሓት መሪዎች ላይ መጣሉ ይታወቃል።

Sep. 17/2021

የዜናዉ ምንጭ Ethiopian Reporter ጋዜጣ ነዉ

Comments