የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ምላሽ ለመስጠት ከ220 በላይ የሕክምና መስጫ እና ለይቶ ማቆያ ማዕከላት ዝግጁ ተደርገዋል

Home Forums Semonegna Stories ኢትዮጵያ ውስጥ የኮቪድ-19 (ኮሮና ቫይረስ) ስርጭትን እና ለመከለከል የሚደረገውን ጥረት ወቅታዊ መረጃ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ምላሽ ለመስጠት ከ220 በላይ የሕክምና መስጫ እና ለይቶ ማቆያ ማዕከላት ዝግጁ ተደርገዋል

#14388
Anonymous
Inactive

የኮሮና ቫይረስ (ኮቪድ-19) ወረርሽኝን ምላሽ ለመስጠት ከ220 በላይ የሕክምና መስጫ እና ለይቶ ማቆያ ማዕከላት ዝግጁ ተደርገዋል

አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – በሀገራችን የኮሮና ቫይረስ (ኮቪድ-19) ወረርሽኝን ምላሽ ለመስጠት ከአንድ መቶ ሺህ በላይ ሰዎችን ሊይዙ የሚችሉ ከ220 በላይ የሕክምናና የለይቶ ማቆያ ማዕከላት ተዘጋጅተዋል።

በኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የሕብረተሰብ ጤና ድንገተኛ አደጋ ማስተባበሪያ ማዕከል የኮቪድ-19 የተቋማት ዝግጁነት ክፍል አስተባባሪ አቶ ኢሳያስ መሠለ እንደገለጹት፥ የኮሮና ቫይረስ በቻይና ዉሃን ከተማ (Wuhan) ከተከሰተ ጀምሮ በሀገራችንም የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ተሠርተዋል። ከዚህም ውስጥ የኮሮና ቫይረስ የተገኘባቸውን ሰዎች የሕክምና መስጫ ማዕከል (treatment centers)፣ የበሽታውን ምልክት የሚያሳዩ ሰዎች የላብራቶሪ ምርመራ ተደርጎላቸው ውጤታቸው እስኪታወቅ ተለይተው የሚቆዩበት (isolation centers) እንዲሁም ከመጋቢት 14 ቀን 2012 ዓ.ም. ጀምሮ ማንኛውም ከውጭ ወደ ሀገር ውስጥ የሚገባ ግለሰብ ለ14 ቀናት ለይቶ ማቆያ መግባት እንዳለበት በተላለፈው ውሳኔ መሠረት የለይቶ ማቆያ ቦታዎችን (quarantine centers) መለየትና ዝግጁ ማድረግ እየተከናወኑ ያሉ ሥራዎች ናቸው።

በዚህም መሠረት ይህ መረጃ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ በአዲስ አበባና በክልሎች ሙሉ በሙሉ ለኮሮና ቫይረስ ህሙማን አገልግሎት እየሰጠ የሚገኘውን የኤካ ኮተቤ ሆስፒታል ጨምሮ ከ10,000 በላይ ሰዎች የሕክምና አገልግሎት መስጠት የሚችሉ ከ40 በላይ ማዕከሎች (treatment centers) ዝግጁ የሆኑ ሲሆን ከ15,000 በላይ ሰዎችን አገልግሎት መስጠት የሚችሉ ከ100 የሚበልጡ የለይቶ ማቆያዎች (isolation centers) እንዲሁም የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎችን ጨምሮ ከ80 በላይ የለይቶ ማቆያዎች (quarantine center) ተዘጋጅተዋል።

ከዚህ ጋር በተያያዘም የኮቪድ-19 ብሔራዊ የድንገተኛ ማዕከል የኢንፌክሽን መከላከልና መቆጣጠር የውሀ፣ ሳኒቴሽንና ሀይጅን (sanitation and hygiene) ክፍል አስተባባሪ ወ/ሮ ኢክራም ሬድዋን እንደተናገሩት፥ ለኮሮና ቫይረስ (የኮቪድ-19) በሽታ በተዘጋጁ የለይቶ ማቆያ እና ሕክምና ማዕከላት ያሉ የውሀ ሳኒቴሽንና ሀይጅን እንዲሁም ኢንፌክሽንን ከመከላከልንና መቆጣጠር አንፃር ያሉ ክፍተቶችን በመለየት ለመሙላት እየተሠራ እንደሚገኝ ገልጸዋል። ይህም ከውሀ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር፣ ከውሀ ልማት ኮሚሽን እና ከአጋር ድርጅቶች በተደረጉ ድጋፎች ሲሆን፥ የውሀ መቆራረጥና እጥረት ያለባቸውን ተቋማት ክፍተት መሙላት፤ የውሀ አቅርቦት መቆራረጥን ለመቀነስ የውሀ ታንከሮችና ፓምፖችን መግጠም፣ ውሀን በከባድ መኪና (truck) ማቅረብ እንዲሁም የእጅ መታጠቢያ እጥረት ባለባቸው የለይቶ ማቆያ እና ሕክምና ማዕከላት ከእጅ ንክኪ የጸዱ በእግር መከፈት የሚችሉ ተንቀሳቃሽ የእጅ መታጠቢያዎች እንዲተከሉ ተደርጓል።

በተጨማሪም ለሁሉም ለይቶ ማቆያ እና ሕክምና ማዕከላት የኢንፌክሽን መከላከልና መቆጣጠር ባለሙያ እና በአዲስ አበባ ለሚገኙ የለይቶ ማቆያ እና ሕክምና ማዕከላት የፀረ-ተህዋሲያን ኬሚካል ርጭት ባለሙያዎች ተመድበዋል። ለነዚህ ባለሙያዎችም የኮቪድ-19 የኢንፌክሽን መከላከልና መቆጣጠር ስልጠና የተሰጠ ሲሆን፥ ባለሙያዎቹም በአጠቃላይ የሚከናወኑ ተግባራት ኢንፌክሽንን ከመከላከልና መቆጣጠር አንጻር በአግባቡ እየተካሄዱ መሆናቸውን በየዕለቱ ይከታላሉ ብለዋል።

በአጠቃላይ በሽታውን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ከሚሠሩ ሥራዎች ባሻገር ሕብረተሰቡ የሚያደርጋቸው ጥንቃቄዎች ለበሽታው ያለመስፋፋት ወሳኝ በመሆናቸው ሕብረተሰቡ ሳይዘናጋ የሚተላለፉ መልዕክቶችን እና መከላከያ መንገዶችን ተግባራዊ በማድረግ የድርሻውን እንዲወጣ አሳስበዋል።

ለተጨማሪ መረጃ በስልክ መስመር 8335 ወይም በ952 በመደወል ወይም የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የኢሜል አድራሻ ephieoc@gmail.com በመጠቀም ወይም ባሉበት ክልል በተዘጋጁ ነፃ የስልክ መስመሮች በመደወል ሪፖርት እንዲያደርጉ ወይም በአካባቢው ለሚገኙ ጤና ተቋማት በስልክ እንዲያሳውቁ ኢንስቲትዩቱ ይጠይቃል።

ምንጭ፦ የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት/ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

EPHI NDMC new website for COVID-19 ለይቶ ማቆያ ማዕከላት