ተሰርዞ የነበረው የ20/80 እና 40/60 የጋራ መኖሪያ ቤቶች ዕጣ ወጣ (የዕድለኞች ስም ዝርዝር)

Home Forums Semonegna Stories በአዲስ አበባ የ51 ሺህ 229 የጋራ መኖሪያ ቤቶች (ኮንዶሚኒየም ቤቶች) የዕድለኞች ስም ዝርዝር ተሰርዞ የነበረው የ20/80 እና 40/60 የጋራ መኖሪያ ቤቶች ዕጣ ወጣ (የዕድለኞች ስም ዝርዝር)

#54149
Semonegna
Keymaster

ተሰርዞ የነበረው የ20/80 እና 40/60 የጋራ መኖሪያ ቤቶች ዕጣ ወጣ ((የዕድለኞች ስም ዝርዝር))

አዲስ አበባ (ኢዜአ) – የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከዚህ ቀደም ተሰርዞ የነበረውን የ20/80 እና የ40/60 የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ዕጣ አወጣ። የ14ኛዉ ዙር የ20/80 እና 3ኛዉ ዙር የ40/60 የጋራ መኖሪያ ቤቶች (condominium houses) ዕጣ የማውጣት ሥነ-ሥርዓት ህዳር 6 ቀን 2015 ዓ.ም ተካሂዷል።

በዕጣ ማውጣት ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ አዳነች አቤቤን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች ተወካዮች በታዛቢነት ተገኝተዋል።

በዕጣው የ20/80 የቤት ልማት ፕሮግራም 18,930 ቤቶች፣ በ40/60 ደግሞ 6,843 ቤቶች እንዲሁም ተጨማሪ 18 ስቱዲዮ ቤቶች በድምሩ 25,791 ቤቶች በዕለቱ ዕጣ ወጥቶባቸዋል።

የጋራ ቤቶች (condominium houses) ዕጣ ሐምሌ 01 ቀን 2014 ዓ.ም ወጥቶ የነበረ ቢሆንም በዕጣው ማውጣት ሂደት በገጠመ ችግር ምክንያት ዕጣው በመሰረዙ ነው አሁን በድጋሚ የዕጣ ማውጣት ሂደት የተከናወነው።

የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዕጣ ማውጣት ሥነ-ሥርዓቱ ላይ እንዳሉት፥ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ከግንባታ እስከ ዕጣ ማውጣት ሂደት ባለፉት ጊዜያት ከውስጥም ሆነ ከውጭ በርካታ ችግሮች አስተናግዷል። ከዚህ አንፃር ዛሬ የወጣው የ20/80 እና 40/60 የጋራ መኖሪያ ቤቶች ዕጣ በርካታ ችግሮችን በማለፍ በስኬት መከናወኑን አንስተዋል።

በተለይ በለውጡ ዋዜማ የሥራ ተቋራጮች ሥራውን አቋርጠው የመጥፋት፣ የመሠረተ ልማት ዝርፊያ የግንባታ ጥራት ችግር፣ የፋይናንስ እጥረትን ጨምሮ ዘርፉ የተወሳሰበ ሂደት ውስጥ ለማለፍ ተገድዷል ነው ያሉት።

የከተማ አስተዳደሩ እነዚህን ውስብስብ ችግሮች ለመፍታት ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከ21 ቢሊዮን ብር በላይ በመበደር ጥረት ሲያደርግ መቆየቱንም እንዲሁ አስታውቀዋል።

ሆኖም ከዚህ በፊት ዕጣ የወጣባቸውን የጋራ ቤቶች ለተጠቃሚዎች ለማድረስ የተደረገው ሙከራ በተለያዩ የሌብነት ተግባራት ምክንያት ሳንካ ገጥሞት እንደነበርም ጠቅሰዋል። ይህ ደግሞ ለረጅም ዓመታት በትዕግስት ሲጠባበቅ ለነበረው ሕዝብ አሳዛኝ ዜና እንደነበር አውስተዋል።

በዕጣ ማውጣት ሂደቱ ከተፈጠረው ችግር ጀርባ የቤት ልማት መርሃ-ግብርን ለግል ጥቅም ማካበቻ ከማድረግ ባለፈ በመንግሥትና በሕዝብ መካከል አለመተማመን ለመፍጠር ያለመ ሴራም እንደነበር ነው የተናገሩት። የከተማ አስተዳደሩ የገጠመውን ችግር ለሕዝብ በግልፅ ይፋ በማድረግ በአጥፊዎች ላይ ተጠያቂነትን ማስፈኑን ጠቅሰዋል።

ተዓማኒነቱ የተረጋገጠ አዲስ የዕጣ ማውጫ ሥርዓት በማልማትም ከዚህ ቀደም ተሰርዞ የነበረው የጋራ መኖሪያ ቤቶች ዕጣ አሁን (ህዳር 6 ቀን 2015 ዓ.ም) በድጋሚ እንዲወጣ መደረጉን ተናግረዋል። የጋራ መኖሪያ ቤቶች ዕጣ በድጋሚ እንዲወጣ ያለመታከት ጥረት ያደረጉ ሰራተኞችና አመራሮችን አመስግነው ባለእድለኞችንም እንኳን ደስ ያላችሁ ብለዋል።

ዛሬ የጋራ መኖርያ ቤት ዕጣ ለደረሳችሁ 25,791 ባለ እድለኞች እንኳን ደስ አላችሁ!!
ለዘመናት በትዕግስት ስትቆጥቡና ስትጠባበቁ የነበራችሁ የ14ኛ ዙር የ20/80 እንዲሁም የ3ኛ ዙር የ40/60 የጋራ መኖርያ ቤት ባለ እድለኞች በሙሉ እንኳን ደስ አላችሁ ለማለት እወዳለሁ!!
ከዚህ ቀደም በቤት የዕጣ አወጣጥ ሂደት በገጠመን የማጭበርበር ችግሮች ምክንያት የእጣ አወጣጥ ሂደቱ ቢዘገይና እክል ቢገጥመውም የህዝብን ሃብት ለማዳን ያደረግነውን ጥረት በመረዳት ከጎናችን ስለሆናችሁና በከፍተኛ የሃላፊነት ስሜት የህግ የበላይነት እንዲከበር በትዕግስትና በማስተዋል እገዛችሁ ላልተለየን የከተማችን ነዋሪዎች በሙሉ ምስጋናችን ላቅ ያለ ነው፡፡
እንዲሁም ለዚህ ስራ ስኬት በትጋት የተሳተፋችሁ ፤በየደረጃው የምትገኙ የስራ ሃላፊዎች፣ አመራሮች ፣ሰራተኞች፣ ባለሙያዎችና የፌደራል ተቋማት ስላበረከታችሁት ታላቅ አስተዋፅኦ በከተማ አሳተዳደሩ ስም ልባዊ ምስጋናዬን ለማቅረብ እወዳለሁ!!
አሁንም የጀመርነውን ከተማችንን እንደ ስሟ ውብና ደማቅ ለነዋሪዎቿ የምትስማማ የማድረግ ስራ ቃላችንን ጠብቀን በመቀጠል ከተማችንን ተወዳዳሪ ብቁና የቱሪስት መዳረሻ የማድረግ ስራ አጠናክረን የምንቀጥል ይሆናል፡፡
ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ህዝቦቿን አብዝቶ ይባርክ!!
ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ

የ14ኛ ዙር የ20/80 የጋራ መኖርያ ቤት ባለ ዕድለኞችን ለማየት ተከታዩን የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (ኢቢሲ) ቴሌግራም ማስፈንጠሪያ ይጫኑ – EBC Telegram Link

ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት

የጋራ መኖሪያ ቤቶች ዕጣ ወጣ