አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የትራንስፖርት አገልግሎት ለመስጠት ተጨማሪ 560 አውቶቡሶች ተሰማሩ

Home Forums Semonegna Stories አዲስ አበባ ከተማን የተመለከቱ ሰሞነኛ ዜናዎችና መረጃዎች አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የትራንስፖርት አገልግሎት ለመስጠት ተጨማሪ 560 አውቶቡሶች ተሰማሩ

#16398
Anonymous
Inactive

አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የትራንስፖርት አገልግሎት ለመስጠት ተጨማሪ 560 አውቶቡሶች ተሰማሩ

አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የሚታየውንና እጅግ ስር የሰደደውን የሕዝብ ትራንስፖርት ችግር በጥቂቱ ለመቅረፍ ተጨማሪ 560 አውቶቡሶች ለአገልግሎት መሰማራታቸውን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አስታውቋል።

“የትራንስፖርት ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ከአውቶብስ አቅርቦት በተጨማሪ ዘመናዊ የትራንስፖርት የመሠረተ ልማት ሥርዓት እንዲዘረጋ በልዩ ትኩረት እየተሠራ ነው” በማለት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ ተናግረዋል።

ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ በኪራይ ወደ ስምሪት የገቡትን እነዚህን 560 አውቶብሶች ሥራ አስጀምረዋል።

በሥነ-ሥርዓቱ ላይ ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ እንደገለጹት፥ በአዲስ አበባ ከተማ የሚታየው የትራንስፖርት ችግር በነዋሪዎች የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እያሳደረ መሆኑን ገልጸዋል።

የትራንስፖርት ችግሩን በተወሰነ ደረጃ ለመፍታት በመንግሥት እና በግሉ ዘርፍ የጋር ትብብር 560 አውቶብሶችን በኪራይ ለሕብረተሰቡ አገልግሎት እንዲሰጡ የከተማ አስተዳደሩ በልዩ ሁኔታ መወሰኑን ወ/ሮ አዳነች አቤቤ ተናግረዋል።

ለዚህም የከተማ አስተዳደሩ ከአሁን ቀደም በየወሩ ለብዙኃን ትራንስፖርት አገልግሎት 58 ሚሊዮን ብር ድጎማ በማድረግ ላይ ሲሆን፤ አሁን ደግሞ ለአውቶቡሶች ኪራይ 63 ሚሊየን ብር በጠቅላላው 121 ሚሊዮን ብር ድጎማ እንደሚያደርግ ምክትል ከንቲባዋ አመልክተዋል።

የትራንስፖርት ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታትም ከአውቶብስ አቅርቦት በተጨማሪ ዘመናዊ የትራንስፖርት የመሠረተ ልማት ሥርዓት እንዲዘረጋ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በልዩ ትኩረት እየተሠራ መሆኑን ወ/ሮ አዳነች አቤቤ ጠቁመዋል። በቀጣይ ሁለት ዓመታትም በ12 ቢሊዮን ብር ወጪ 3 ሺህ የሚሆኑ አውቶብሶችን በግዢ ለማስገባት የከተማ አስተዳደሩ በሂደት ላይ መሆኑንም ምክትል ከንቲባዋ ተናግረዋል። ወደፊትም የነዋሪዎቻችንን ችግር በቅርበት አዳምጠን እና ተረድተን ተጨባጭ መፍትሄ የመስጠቱን ሥራ አጠናክረን እንቀጥላለን ብለዋል – ወ/ሮ አዳነች።

በኪራይ ወደ ስምሪት የ560 አውቶብሶች ከጥቅምት 9 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ ሥራ የሚጀምሩ ሲሆን ለአንድ ሳምንት ያህል ለሁሉም የከተማዋ ነዋሪ የነፃ አገልግሎት እንደሚሰጡ ተገልጿል።

በሥነ-ሥርዓቱ ላይ ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤን ጨምሮ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የመንግሥት አገልግሎት ሰጪ አስተባባሪ አቶ ጃንጥራር አባይ እና ሌሎች የከተማዋ ከፍተኛ የሥራ ሀላፊዎች ተገኝተዋል።

ምንጭ፦ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽህፈት ቤት የፕሬስ ሴክሪታሪያት/ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

ተጨማሪ 560 አውቶቡሶች ተሰማሩ