የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ ኤጀንሲ ለ18 ወራት የሚበቃ የመድኃኒት ክምችት መኖሩን ገለጸ

Home Forums Semonegna Stories ኢትዮጵያ ውስጥ የኮቪድ-19 (ኮሮና ቫይረስ) ስርጭትን እና ለመከለከል የሚደረገውን ጥረት ወቅታዊ መረጃ የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ ኤጀንሲ ለ18 ወራት የሚበቃ የመድኃኒት ክምችት መኖሩን ገለጸ

#14479
Anonymous
Inactive

የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ ኤጀንሲ ለ18 ወራት የሚበቃ የመድኃኒት ክምችት መኖሩን ገለጸ
ለለይቶ ማቆያዎች የሕክምና ቁሳቁሶች ተሟልቶ እየቀረበ እንደሚገኝ ተጠቁሟል

አዲስ አበባ (አዲስ ዘመን) – የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ ኤጀንሲ ለ18 ወራት የሚበቃ የመድኃኒት ክምችት ለመያዝ እየሠራ መሆኑ ተገለጸ። በፌደራልና በክልል ደረጃ ለሚገኙ ለይቶ ማቆያዎች የሕክምና ቁሳቁሶች ተሟልቶ እየቀረበላቸው እንደሚገኝም ተጠቁሟል።

በኤጀንሲው የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር ወ/ሮ አድና በሬ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፥ ኤጀንሲው በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ሳቢያ በሀገሪቱ የመድኃኒት አቅርቦት እጥረት እንዳይከሰት ከወዲሁ ለ18 ወራት የሚበቃ የመድኃኒት ክምችት ለመያዝ እየሠራ ይገኛል።

እንደ ዳይሬክተሯ ማብራሪያ፤ ከ80 በመቶ በላይ የሚሆነው የመድኃኒት አቅርቦት ከውጭ የሚገባ በመሆኑ በሀገሪቱ የመድኃኒት አቅርቦት እጥረት አንዴ ከተከሰተ የአቅርቦት ሰንሰለቱን ለመመለስ ጊዜ ስለሚወስድ ችግሩን በፍጥነት ለመቅረፍ አዳጋች ያደርገዋል። ኤጀንሲው ችግሩን ከግምት ውስጥ በማስገባት ቫይረሱ ወደ ሀገሪቱ ቢገባ በመድኃኒት አቅርቦቱ ላይ ሊያሳድር የሚችለውን ተጽኖ ታሳቢ በማድረግ፥ ኮሚቴ ተቋቁሞ በመጋዘን ምን ያህል የመድኃኒት ክምችት እንዳለ፤ ከወርሃዊ ፍጆታው አንጻር በመጋዘንና በመጓጓዝ ላይ ያለው መድኃኒት ለምን ያህል ጊዜ እንደሚበቃ፣ መጠናቸውን፣ የትኛው መድኃኒት ቀድሞ መግባት እንዳለበት፣ እስከ መቼ መድኃኒቶቹ ወደ አገር ውስጥ ሊገቡ እንደሚችሉ ቀደም ብሎ ጥናት ተደርጓል።

ወ/ሮ አድና ኮሚቴው ቫይረሱ በሀገሪቱ ከተከሰተ በኋላም ከተመላላሽ ታካሚዎች ባሻገር በተለይ ተከታታይ መድኃኒት የሚወስዱ ወገኖች እጥረት እንዳያጋጥማቸው፣ በመጋዘንና በመጓጓዝ ላይ ያለው መድኃኒት ለነዚህ ወገኖች አቅርቦት ሳይቆራረጥ ምን ያህል ጊዜ ሊያስኬድ ይችላል የሚለው ላይም በድጋሚ ጥናት ማካሄዱን ተናግረዋል።

ኤጀንሲው በጥናቱ መሠረት የመድኃኒቶቹን የአገልግሎት ዕድሜ ታሳቢ በማድረግ ለ18 ወራት የሚበቃ የመድኃኒት ክምችት ለመያዝ እየሠራ እንደሚገኝ ገልጸው፥ በተለይ የስኳር፣ የደም ግፊት፣ የአስም፣ የልብ ህመምተኞች በተከታታይ ከሚወስዷቸው መድኃኒቶች በተጨማሪ ኤችአይቪ (HIV) በደማቸው የሚገኝባቸው ወገኖች የሚወስዷቸው የፕሮግራም መድኃኒቶችን ለ18 ወራት የሚበቃ ክምችት ለመያዝ ታሳቢ ተደርጎ ግዢ እንዲፈጸም፣ በመጓጓዝ ላይ ያሉት በወቅቱ እንዲገቡና በመጋዘን ተከማችተው ያሉ መድኃኒቶችም በወቅቱ ወደ ጤና ተቋማቱ ተልከው ለህመምተኞች እንዲደርስ የማድረግ ሥራ እየተሠራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ወ/ሮ አድና የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በጤና ቀውስነቱ እስከመቼ ድረስ እንደሚቀጥል ስለማይታወቅ የመድኃኒት አቅርቦት እጥረቱ ተከስቶ ችግር ውስጥ ከመገባቱ በፊት የመድኃኒት ክምችቱን ማሳደግ ላይ መሠራቱ ዘርፈ ብዙ ጥቅም እንዳለው ጠቁመው፥ ቀደም ሲል በውል የታሰሩ የመድኃኒት ግዢዎች በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ዋጋ ከመጨመር ባለፈ በውሉ መሠረት ድርጅቶቹ ለማቅረብ እያመነቱ በመሆኑ በተፈለገው መጠን መድኃኒቶቹን ለማከማቸት እንቅፋት ሊፈጥር እንደሚችል ተናግረዋል።

በተያያዘ ዜና የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ ኤጀንሲ የኮሮና ቫይረስ በሀገሪቱ ከተከሰተ ጊዜ ጀምሮ ወረርሽኙን ለመከላከል የሚያስችሉ የሕክምና ግብዓቶችን እያሠራጨ እንደሚገኝ ዳይሬክተሯ ገልጸው፥ ኤጀንሲው የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በሚያቀርበው ጥያቄ መሠረት በፌዴራልና በክልል ደረጃ ለሚገኙ ለይቶ ማቆያዎች ሙሉ ለሙሉ የሕክምና ቁሳቁሶችን አሟልቶ እያቀረበ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት/ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ ኤጀንሲ Ethiopian Pharmaceuticals Supply Agency EPSA